የቀደመችው መንገድ
ከአንድ ጓደኛችን ቤት
ተሰብስበን ስንጨዋወት፥ አንዳንዶቻችን መጽሔቶችንና አልበሞችን እናገላብጥ ነበር፡፡ ከመካከላችንም አንዱ ወንድም የተለያየ ጌጠኛ
ቅርጽ የተሰጣቸው 50 የመስቀል ምስሎች የተሣሉበትን አንድ ገጽ ወረቀት አገኘና በአድናቆት አሳየን፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎች
የተራቀቀ ሙያቸውን የገለጹባቸው ውበቶች ይታዩባቸው ነበር፡፡ የምስሎቹ ብዛት በአንድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ካየናቸው
የመስቀል ምስሎች በ30 ቍጥር ብልጫ ነበረው፡፡ አንዱ ጓደኛችን “ከእነዚህ መካከል ትክክለኛው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል
የትኛው ነው?” አለና ጠየቀ፡፡ እርስ በርስ ተያየንና ተሣሣቅን፡፡ ሌላውም ሌላ ጥያቄ አከለበት፡፡ “ከዕንጨት፥ ከድንጋይ፥
ከብረታ ብረት፥ ከከበሩ ማዕድናት ከተፈበረኩት መካከል ክብር ያለው መስቀል የትኛው ነው?” ማንም መልስ አልሰጠም፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ
መስቀል ሲባል ወደ ሰው አእምሮ ፈጥኖ የሚመጣው ትውስታ እንደ “ተ” ያለ ቅርጽና እርሱን ለማስዋብ በባለሙያዎች የሚጨመርበት
ሐረግ (ጠልሰም) ነው፡፡ ግን ይህም ሆነ ያ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ ለምን፥ እንዴት፥
ቢባል በዓለም ላይ መስቀል በሚል ስም የምናየው ምስል ሁሉ ሌላ ባለቤት አለው፡፡ አንጥረኞች፥ ጠራቢዎች፥ ቀራጺዎች፥ ዐናጺዎች፥
አምራች ድርጅቶች፥ ላመረቷቸው መስቀሎች የመጀመሪያ ባለቤቶች ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ላይ የገዙ ሰዎችም ገንዘብ ያወጡበት ነውና የኔ
የሚሉት የግል ንብረታቸው ነው፡፡ እነርሱም ሊሸጡት፥ ሊለውጡት፥ ሊያጌጡበትም መብት አላቸው፡፡ የጌታ መስቀል ግን አይሸጥም
አይለወጥም፡፡ ሸጠው ለወጠው የሚለው ማስረጃ የለም፡፡ ያ መስቀል አሁንም የራሱ ነው፡፡