በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ
የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ
አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡
አለቃ ታየ ገብረ
ማርያም (1853 - 1916 ዓ.ም.)
አይሁድ መሲሑን ይጠባበቁ የነበሩ ሕዝብ ናቸው፤
መሲሑ ሲመጣ ግን አልተቀበሉትም፡፡ የመሲሑን ደቀ መዛሙርትም አሳድደዋል፡፡ እነርሱን መስሎ የሚኖረውን ሰው እውነተኛ አይሁዳዊ ሲሉ፥
ዐዲስና እንግዳ ትምህርትን ሳያመጣ በመጽሐፋቸው የተገለጠውንና እነርሱ ያላስተዋሉትን እውነት የሚያምነውንና የሚኖረውን የመሲሑን
ተከታይ ደግሞ መናፍቅ እያሉ ሲኰንኑ ኖረዋል፡፡
ሳውል፥ በጊዜው በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ
የሕግ መምህር በነበረው በገማልያል እግር ሥር ተቀምጦ የተማረ ሊቅ እንደ መሆኑ በዚያው ሥርዐት ሲኖር እጅግ የተከበረ ሰው
ነበረ (ፊል. 3፥5-6)፡፡ ክርስቶስ ከተገለጠለትና በወንጌል አምኖ የእርሱው አገልጋይ ከሆነ በኋላ ግን፥ የቀድሞ ክብሩን
ዐጥቶ አሳዳጁ ሲሰደድና ሲንገላታ፥ አለሥራውም ክፉ ስም ሲወጣለት ነበር፡፡ ቀድሞ ያከበሩት ወገኖች፥ “ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥
የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው” (ሐ.ሥ. 24፥1-9) ሲሉ
በሐሰት ከሰዉታል፡፡ እርሱም ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ፥ “በሕጉ
ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፡፡ እነዚህም
ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት ጻድቃንም ዐመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ ”
(ቊጥር 10-21) ብሏል፡፡